Загрузка страницы

ትንቢተ ኢሳይያስ - Amharic Audio Bible: Isaiah - (All Book Ch, 1-66)

6:1፤ ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።
2፤ ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር።
3፤ አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር።
4፤ የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፥ ቤቱንም ጢስ ሞላበት።
5፤ እኔም። ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ።
6፤ ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ።
7፤ አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ።
8፤ የጌታንም ድምፅ። ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም። እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ።
9፤ እርሱም። ሂድ፥ ይህን ሕዝብ። መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው።
10፤ በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ።
11፤ እኔም። ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? አልሁ። እርሱም መልሶ እንዲህ አለ። ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ፥ ቤቶችም ሰው አልቦ እስኪሆኑ ምድርም ፈጽሞ ባድማ ሆና እስክትቀር ድረስ፥
12፤ እግዚአብሔርም ሰዎችን እስኪያርቅ፥ በምድርም መካከል ውድማው መሬት እስኪበዛ ድረስ ነው።
13፤ በእርስዋም ዘንድ አሥረኛ እጅ ቀርቶ እንደ ሆነ እርሱ ደግሞ ይቃጠላል፤ በተቈረጡ ጊዜ ጉቶቻቸው እንደ ቀሩ እንደ ግራርና እንደ ኮምበል ዛፍ ሆኖ፥ ጉቶው የተቀደሰ ዘር ይሆናል።

53:1፤ የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል?
2፤ በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም።
3፤ የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም።
4፤ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።
5፤ እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።
6፤ እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።
7፤ ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
8፤ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?
9፤ ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገንበትም ነበር።
10፤ እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈከደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።
11፤ ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሰከማል።
12፤ ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።

66:1፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው?
2፤ እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።
3፤ በሬን የሚያርድልኝ ሰውን እንደሚገድል ነው፤ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደሚሰብር ነው፤ የእህልን ቍርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው፤ ዕጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል፤
4፤ እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን እመርጣለሁ፥ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ፤ በፊቴ ክፉ ነገርን አደረጉ፥ ያልወደድሁትንም መረጡ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሱልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝምና።
5፤ በቃሉ የምትንቀጠቀጡ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። የጠሉአችሁ ስለ ስሜም ያባረሩአችሁ ወንድሞቻችሁ። ደስታችሁን እናይ ዘንድ እግዚአብሔር ይክበር ብለዋል፤ ነገር ግን ያፍራሉ።
6፤ የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹ ላይ ፍዳን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ድምፅ ተሰምቶአል።
7፤ ሳታምጥ ወለደች፤ ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጅን ወለደች።
8፤ ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና።
9፤ በውኑ ወደ መውለድ የማደርስ እኔ አላስወልድምን? ይላል እግዚአብሔር፤ የማስወልድስ ማኅፀንን እኔ እዘጋለሁን? ይላል አምላክሽ።
10፤ እናንተ የምትወድዱአት ሁሉ፥ ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሤትን አድርጉ፥ ስለ እርስዋም ደስ ይበላችሁ፤ እናንተም የምታለቅሱላት ሁሉ፥ ከእርስዋ ጋር በደስታ ሐሤትን አድርጉ፥
11፤ ትጠቡ ዘንድ ከማጽናናትዋም ጡት ትጠግቡ ዘንድ፤ እጅግ ጠጥታችሁ በክብርዋ ሙላት ደስ ይላችሁ ዘንድ።
12፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ከዚያም ትጠባላችሁ፥ በጫንቃ ላይ ይሸከሙአችኋል በጕልበትም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሉአችኋል።
13፤ እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ትጽናናላችሁ።
14፤ ታያላችሁ፥ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፥ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፤ የእግዚአብሔርም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፥ በጠላቶቹም ላይ ይቈጣል።
15፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር መዓቱን በቍጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ ከእሳት ጋር ይመጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ።
16፤ እግዚአብሔርም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፉ ይፈርዳል፤ በእግዚአብሔርም ተወግተው የሞቱት ይበዛሉ።
17፤ በመካከላቸው ያለውን አንዱን ተከትለው ወደ ገነቱ ይገቡ ዘንድ ሰውነታቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፥ የእሪያንም ሥጋ አስጸያፊ ነገርንም አይጥንም የሚበሉ በአንድነት ይጠፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
18፤ ሥራቸውንና አሳባቸውን አውቄአለሁና፤ አሕዛብንና ልሳናትን ሁሉ የምሰበስብበት ጊዜ ይደርሳል፥ እነርሱም ይመጣሉ ክብሬንም ያያሉ።
19፤ በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፥ ከእነርሱም የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ ወደ ፉጥ ወደ ሉድ ወደ ሞሳሕ ወደ ቶቤል ወደ ያዋን በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፥ በአሕዛብም መካከል ክብሬንም ይናገራሉ።
20፤ የእስራኤል ልጆች ቍርባናቸውን በጥሩ ዕቃ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁ ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎች በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር።
21፤ ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
22፤ እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
23፤ እንዲህ ይሆናል፤ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ይሰግድ ዘንድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።
24፤ ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።

Видео ትንቢተ ኢሳይያስ - Amharic Audio Bible: Isaiah - (All Book Ch, 1-66) канала SERGIO ALEO
Показать
Комментарии отсутствуют
Введите заголовок:

Введите адрес ссылки:

Введите адрес видео с YouTube:

Зарегистрируйтесь или войдите с
Информация о видео
1 ноября 2019 г. 19:22:59
03:52:58
Яндекс.Метрика